አንተ የምትሰራቸውን ማንም ሊሰራ አይችልም

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ እየተመላለሰ ባስተማረው ትምሕርትና ባደረጋቸው ታላላቅ ገቢረ ተአምራት ያመኑና አምላክነቱን የተቀበሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። በአንጻሩ ትምሕርቱንና ገቢረ ተአምራቱን ተመልክተው ከራሳቸው ጥቅም አንጻር በማየት የጥቅማቸው ተቀናቃኝ የመጣ መስሏቸው የሚቃወሙትም ነበሩ። ጌታችን በአንድ ወቅት እንደነዚህ አይነቱን ከጭፍን ጥላቻ እንዲላቀቁና የሚሰራውን ሥራ አይተው በእርሱ እንዲያምኑ በእኔ ባታምኑ በስራዬ እመኑ ብሏቸዋል። ሢሰራ የነበረው ሥራ ስለ እርሱ ማንነትና ምንነት የሚገልጹልን ምስክሮች ናቸው። የክርስቶስን ሥራና ትምሕርት በማየት እርሱ ነቢያት በትንቢት የተናገሩለት መሲህ መሆኑን ከተቀበሉትና ከመሰከሩለት ውስጥ ከተቃዋሚዎቹ ወገን የነበረው ፈሪሳዊው ኒቆዲሞስ አንዱና ዋነኛው ነው። ዮሐ 3፥1

ኒቆዲሞስ በአይሁድ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ የሚያሰጠውን ፈሪሳዊነት ላይ የደረሰ ታላቅ ሰው ነው። ተጠያቂ ምሁር፣ የሐይማኖት መሪ፣ ሕገ ኦሪት ጠንቅቆ የሚያውቅ ተርጓሚና ዳኝነትን እስከመስጠት የደረሰ የከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰናሐድሬም ጉባኤ አባል ነበር። በሃብት በኩል ችግር የሌለበት ባለጸጋ በመሆኑ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በህዝብ ዘንድ እጅግ በጣም የተከበረ እንዲሆን አድርገውታል። በስብእናው በዘመኑ ከነበሩ ከብዙ ፈሪሳዊያን የተለየ አመለካከት የነበረው ፈሪሳዊ ነበር። ብዙዎች ለራሳቸው ክብር ሥርዓት ሲጨነቁ የእግዚአብሔርን ክብር ሲዘነጉ ታይተዋል። ጌታችን በፊት ለፊታቸው ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት እያደረገ ሳያምኑበት እንድናምንብህ ምን ምልክት ታሳየናለህ ብለው እንደገና ይጠይቁት የነበረው ከቅንነት በመነሳት አልነበረም። ኒቆዲሞስ ግን ቀና የሆነ አመለካከት የነበረው ሰው ስለነበር የክርስቶስ ሥራ መሲህነቱን ሳይጠራጠር እንዲቀበል አድርጐታል። ሌሎቹ ፈሪሳዊያን ግን የእነርሱ አለማመን ሳይንሳቸው የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ አዳኝነቱን አንዳይቀበል በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ ከምኩራብ እንዲሰደድ ከማሕበራዊ ሕይወትም እንዲለይ አውጀዋል።

ኒቆዲሞስ ጠንቃቃና አስተዋይ የሆነ ሰው ነው። ጥንቃቄ ይደግፍሃል ማስተዋልም ይጋርድሃል ተብሎ እንደተጻፈ እውቀቱ ጠንቃቃና አስተዋይ ያደረገው ምሑር ነው። በፍርድ ቤት በነበረው ውሎ ስለክርስቶስ የሚሰማው ብዙ ነገር አለ። የተወራውን ወሬ ብቻ ይዞ ክርስቶስን ወደ መጥላት አልሄደም። ክርስቶስ የሚሰራውን ሥራ በነበረው ኦሪታዊ ምሑርነቱ መረመረ። እውነትን አወቀ። ጓደኞቹ የሚቃወሙትንና የሚያሳድዱትን ጌታን ፈልጎ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ አገኘውም። «እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንደመጣህ አናውቃለን» ዮሐ 3፣2 በማለት አዳኝነቱን ለራሱ ለባለቤቱ መስክሯል። ሌሎች ግን የክብራቸው ተሻሚ ስለመሰላቸው ገና ሲያዩት ዓይናቸው በቅንዓት ደም ይመስል ነበር። ስለእርሱ የሚናገሩት ከእርሱ ያዩትንና ስለእርሱ የሰሙትን ሳይሆን ከጥላቻ የተነሣ ከገሊላ ነቢይ አንዴት ይወጣል ከሚል የብሄርተኝነትና የጎጠኝነት አመለካከት ነበር። እውነትን እንዳይቀበሉ ልቦናቸው ታውሮ ነበር። ኒቆዲሞስ ግን ሰውን ከተወለደበት ቦታ አንጻር ከመጥላት ጠባብ አመለካከት የወጣ ሰው ስለነበር የአይሁድ ጉባኤ በጭፍንነትና በጥላቻ ተሞልቶ በክርስቶስ ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ እንደ ወንጀለኛ ሲመለከቱት ‹‹ሕጋችን አሰቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንም እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?›› ዘዳ 1፤16 በማለት ከሕግ መጽሐፍ በመጥቀስ ስለክርስቶስ ተከራክሯል። ዮሐ 7፣50

ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን በሚያስተምርበት ጊዜ ከሕዝብ ጋር ሆኖ ለመማር የአይሁድ አዋጅ ቢያስፈራውም፣ ባለጸጋና ምሁረ ኦሪት ከመሆኑ የተነሳ ከሕዝብ ጋር እንዳላዋቂ ሆኖ ለመማር ፈተና ቢሆንበትም በሌሊት ማንም ሳያየው ወደ ጌታ እየሄደ እርሱ ማንም ሊሰራ የማይችለውን ሥራ የሚሰራ መሲህ መሆኑን ተረዳ። የተማረ ሊቅ ቢሆንም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን አላዋቂነቱን ተረዳ። በትህናም ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን ብሎ ለመማር ራሱን ዝቅ አድርጎ ቀርቧል።ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም›› የሚለውን የምስጢረ ጥምቀት ትምህርት ሲያስተምር ኒቆዲሞስ በሚገባ የተረዳው መልሶ መላልሶ ያልተረዳውን በመጠየቁ እንጂ ሳይገባው የገባው መስሎ ሊቅ ነኝ ብሎ በመገኘቱ አይደለም። መሲህ ክርስቶስ የመጣበትንም አላማ ‹‹ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ አንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል›› ብሎ ጌታችን ነግሮት ነበርና ይህን ታላቅ የማዳን ሥራ በዓይኑ ለማየት በቃ። ከዚህም ሌላ ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ሥጋውን ከመስቀል በክብር አውርዶ ገንዞ ለመቅበር የታደለ ሰው ለመሆን መብቃቱን ቅዱስ ዮሐንስ መስክሮለታል። ዮሐ 19፥39

‹‹ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢያተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ ሰው›› መዝ 1፥1 እንዲል ኒቆዲሞስ ለማህበራዊ ህይወቱ ቅድሚያ በመስጠት፣ ለክብሩ በመጨነቅ፣ ከክፉዎች ጋር ያልመከረ ከሥራቸውም ጋር ያልተባበረ ምስጉን ነው። ኒቆዲሞስ የክርስቶስን ሥራ አስተውሎ የእግዚአብሔር መሆኑን አመነ። እኛም እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚሰራውን ሥራ ስናስተውል ፍጹም አማኞች እንሆናለን። የእግዚአብሔር ሥራ ለእኛ ወደ እርሱ የምንቀርብባቸው ድልድዮች ናቸው። እግዚአብሔር እንደኒቆዲሞስ ማስተዋሉንና ጥበቡን ያድለን።አሜን!

Donate