ቤቴን የንግድ ቤት አታድርጉት

...

ለስሙ ክብር ምስጋና ይሁንና ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ አለም መጥቶ በምድር ላይ በሚመላለስበት ጊዜ በቤተ መቅደስና በምኩራብ እየተገኘ ወንጌልን ሰብኳል። የተለያዩ ገቢረ ተአምራቶችን በነዚህ ሥፍራዎች ተገኝቶ ፈጽሟል። በአሥራ ሁለት ዓመቱ በዓል ለማክበር ከእመቤታችንና ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ሄዶ ነበር። በዓሉን አክብረው እነርሱ ሲመለሱ እርሱ ግን ከዚያው ከቤተ መቅደስ ቀርቶ ነበር። እነርሱም ፈልገውት ባጡት ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ሲመለሱ በመቅደስ ውስጥ በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት። እመቤታችን ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረክብን በማለት ምን ያህል ስለጠፋባቸው እንደተጨነቁና እንደፈለጉት ስትነግረው እርሱ ግን «ስለምን ፈለጋችሁኝ በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?» ሉቃ 2፥49 በማለት መቅደስ የእግዚአብሔር ቤት መሆኑን ተናግሯል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ «የሠራዊት አምላክ ሆይ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባይ ትወዳለች ትናፍቅማለች» መዝ 83፥1 እንዲል የእግዚአብሔር የክብር መገለጫ ይሆኑ ዘንድ ከተመረጡት አንዱ መቅደስ ነው።

የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ያስፈልገዋል ብሎ ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ለሙሴ «በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ» ዘጸ 25፥7 ብሎ ባዘዘው መሰረት ተንቀሳቃሽ መቅደስ ከድንኳን ሰርተው ነበር። ይቺም ድንኳን ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝባት ስለነበረች የመገናኛ ድንኳን የሚል ሰያሜ ተሰጥቷት ነበር። «እግዚአብሔርን የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበረ።»ዘጸ 33፥7 ይቺም ድንኳን የምትዘረጋና የምትተጣጠፍ ስለነበረች በጉዟቸው ላይ ለነበራቸው አምልኮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች። እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ አገልግሎት ሰጥታለች። ዳዊት ግን የእግዚአብሔር ታቦት በድንኳን እርሱ ግን ከዝግባ በተሰራ ቤት መቀመጡን ተመልክቶ አዘነ። በመንፈሳዊ ቅንዓት ተነሳስቶ ለእግዚአብሔር ቤትን ለመስራት ወደደ።መዝ 131፥2 ሁሉ የሚሆነው በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና በጾም በጸሎት ተወስኖ ቢጠይቅም ቤቴን አንተ አትሰራም ቤቴን የሚሰራው ከአብራክህ የሚከፈለው ልጅህ ነው ተብሎ ቤተ መቅደሱን እንዳይሰራ ተከልክሏል። በዚህም መሰረት ቤቱን ለመስራት ልጁ ሰሎሞን ተመርጧል።

ሰሎሞንም ለዚህ ጸጋ በመብቃቱ ተደስቶ እጅግ በጣም የሚያምርና ውብ የሆነ ቤተ መቅደስን ሰርቷል። እግዚአብሔርም በመቅደሱ ተገልጦ አነጋግሮታል። «በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናኽን ሰምቻለሁ። ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሰራኸውን ቀድሻለሁ። ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ በዚያ ይሆናሉ»1ኛ ነገ 9፥1 ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶለታል። እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን ሲሰጠው ቃል ኪዳኑን የሚጠብቀውና የሚያጸናው ሕግና ሥርዓቱ እስከተጠበቀ ድረስ መሆኑንም ሲነግረው «የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርአቴን ባትጠብቁ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታመልኩ ብትሰግዱላቸውም እሥራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ። ለስሜ የቀደሰኩትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ። እስራኤልም በአህዛብ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ» 1ነገ 9፥7 ብሏል። እሥራኤል ሥርአቱንና ሕጉን ባፈረሱ ጊዜ ይህ የአምልኮ ሥፍራ በእሳት ሲጋይ ሕዝቡም ለምርኮ ተዳርጓል።

በምርኮ የነበሩ እሥራኤላዊያን ሐይማኖታቸውንና ባሕላቸውን እንዳይረሱ በየአካባቢያቸው ምኩራብ ሰሩ። በእሥራኤላዊያን ታሪክ ውስጥ ምኩራብ መሰራት የተጀመረው በባቢሎን ነው። አይሁድ ባሕላቸውን ታሪካቸውንና አምልኮታቸውን ተሰባስበው ይፈጽሙት የነበረው በምኩራብ ውስጥ ነበረ። በዕለተ ሰንበት እየተገኙ የሕጉ መጽሐፍ በሊቃውንቱ እየተነበበላቸው በባዕድ አገር የተወለዱት ሕጻናት ማንነታቸውን እንዲያውቁ የሚደረጉት በምኩራብ ውስጥ በሚሰጥ ትምህርት ነበር። የአምልኮታቸውንም ሥርዓት በዚሁ ይፈጽሙ ነበር። ከሰባ ዓመት ግዞት በኋላ ወደ አገራቸው ሲገቡ በነህምያ አስተባባሪነት የኢየሩሳሌም ቅጥር ሲሰራ፣ ቤተ መቅደሱ ሲታነጽ በተለያዩ አካባቢዎች ምኩራብ ተሰርተው አምልኮታቸውን ይፈጽሙ እንደ ነበር በቅዱስ ወንጌል ተጽፏል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በምኩራብ ውስጥ ብዙ ማስተማሩን፣ ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራትን መፈጸሙን ወንጌላውያኑ ጽፈውታል።

አንድ ነገር ከተዘጋጀበት ዓላማ ውጭ አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ ዓላማውን ይስታል። ቤተ መቅደሱም ሆነ ምኩራቡ የተሰራበት ዋና ዓላማ የእግዚአብሔር ክብር እንዲነገርባቸውና እንዲመሰገንበት ነው። ይሁን እንጂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እዚህ አለም በመጣ ጊዜ ቤተ መቅደሱ የእግዚአብሔር ክብር የሚነገርበት ሥፍራ መሆኑ ቀርቶ የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ፣ ሥጋዊ ገበያ የሚካሄድበት ሆኖ ተገኘ። ሻጭና ለዋጭ የሚጨቃጨቅበት፣ ንግዱ የደራበት ሆነ። መንፈሳዊው ዓላማ ተዘንግቶ ሥጋዊ ዓላማ በተቀደሰው ሥፍራ ቦታውን ይዞ ተገኘ። ያን ጊዜ ስለ ቤቱ ቀና። የገመድ ጅራፍ አዘጋጅቶ በጎቹንም በሬዎቹንም ከመቅደስ አወጣቸው፤ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጪዎቹንም ይህን ከዚህ ወሰዱ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ብሎ ገሰጻቸው።

እግዚአብሔር ለመመስገኛ ማደሪያ ይሆን ዘንድ ከመረጠው ውስጥ አንዱ ሰው ነው። ሰው የተፈጠረበት ዋናው ዓለማ እግዚአብሔርን አመስግኖ ክብሩን ይወርስ ዘንድ ነው። ሰው ለተፈጠረበት ዓለማ ራሱን ዝግጁ ካደረገ የእግዚአብሔር ማደሪያ ይሆናል። እግዚአብሔርን የሚያከብርና የሚያመሰግን ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው። ሐዋሪያው «የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል የእግዚአብሔር መቅደስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ» 1ቆሮ 3፥16፥17 መባሉ ለዚህ ነው። አንድ ክርስቲያን በሥላሴ ስም ተጠምቆ፥ በቅብዓ ሜሮን ከብሮ፥ ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን ከተቀበለና ለዘላለማዊ ሕይወት ራሱን ወደ እግዚአብሔር ካቀረበ ሰውነቱን በቅድስና ሊመራ ያስፈልጋል። እርሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሆኗል። መልካም የሆኑ የመንፈስ ፍሬዎች የተባሉትን ፍቅር፣ ሰላም፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ራስን መግዛት፣ ትዕግስት፣ የመሳሰሉትን የመንፈስ ፍሬዎች ማፍራት ይጠበቅበታል። ገላ 5፥22 መልካም ፍሬ የማያፈራ ሕይወት ከሆነ ግን የእግዚአብሔር ቤት መሆን አይችልም። የእግዚአብሔር ቤት ከኃጢያት ንግድ ነጻ የሆነ ሊሆን ይገባዋል። ክፋት፣ ስድብ፣ ዝሙት፣ አድመኝነት፣ ተንኮልን የመሳሰሉ የሥጋ ሥራዎች ሁሉ የኃጢያት ሸቀጣ ሸቀጦች ናቸው።

ንስሐ በመግባት ሕይወታችንን በቅድስና ብንመራ የእግዚአብሔር መቅደስ ለመሆን እንችላለን። በተቀደሰ ሕይወት ለመኖር እንድንችል እግዚአብሔር ሁላችንንም ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን!

Donate